የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሸሪዓን መሰረት አድርገው ከተቋቋሙ ባንኮች ከፍተኛ እውቅናን እያገኘ ከመጣው ዘምዘም ባንክ ጋር በትብብር ለመስራት የሚስያስችለውን ስምምነት ፈፅሟል። ስምምነቱ የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ በተለያየ አማራጭ በሚቀርብ የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ ከማድረጉም በላይ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመማር ማስተማር፣ ምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎች ጋር በአጋርነት መስራት የሚያስችለው መሆኑ ተነግሯል።
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ‘’አማራጭ የባንክ አገልግሎቶችን እና አካታች የባንክ ስርዓትን ይዞ ከመጣው ዘምዘም ባንክ ጋር በትብብር መስራት ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በርካታ ጠቀሜታ ይኖረዋል’’ ብለዋል። የባንክ ኢንደስትሪ በፍጥነት እያደገ መምጣቱን የጠቆሙት ፕሬዝዳንቷ ዘመኑን የሚዋጅ እንዲሁም የተገልጋዩን ፍላጎት ማእከል ያደረገ አሰራሮችን መዘርጋት የግድ እየሆነ መጥቷል ብለዋል።
ዶ/ር ኡባህ አክለውም ከዘምዘም ባንክ ጋር የተደረሰው ስምምነት ዘርፈ ብዙ ተቋማዊ ፋይዳ እንዳለው በመጠቆም በተለይ ተማሪዎችን የተግባር ትምህርት እንዲያገኙ በማድረግ፣ ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የተለያዩ የብድር አማራጮችን በማመቻቸት እና ዩኒቨርሲቲው ለሚሳተፍባቸው ዘርፈ ብዙ ማህበረሰብ አቀፍ ስራዎች ድጋፍ በማድረግ እገዛ የሚያደርግ መሆኑ ተናግረዋል።
ስምምነቱን ለመፈፀም የተገኙት የዘምዘም ባንክን ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አብደላ አደም በበኩላቸው ‘’ዘምዘም ባንክ ከዩኒቨርሲቲው የትኩረት መስኮች ውስጥ አንዱ በሆነው ቢዝነስ እና ኢኮኖሚክስ ዘርፍ ሰፊ የትብብር ስራዎችን የመስራት እቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል።
Share This News