Logo
News Photo

የእንኳን ደስ አላችው መልክት ከድሬደዋ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም

ሀገራችን ኢትዮጲያ በተፈጥሮ ፀጋዎቿ የታደለች እንዲሁም በተለያዩ መልክአ ምድሮቿ እና ህብረ ብሔራዊ ህዝቦች ያጌጠች፣ ታሪክ በተለያየ ኩነቶች የሚዘክራት፣ ቅኝ ገዢዎችን አሳፍራ ቅኝ ሳትገዛ የኖረች፣ የመላው አፍሪካውያን የነፃነት ቀንዲል ጥንታዊ የሰው ዘር መገኛ ውብ ሀገር ናት፡፡
ሀገራችን ያላትን ፀጋ ለመቀራመት ቅኝ ገዢዎች ቢያማትሩም የአንድነታችንን ክንድ መቋቋም ተስኗቸው አፍረው ተመልሰዋል፡፡ ፊት ለፊት ገጥመው አንበርክከው ሊመዘብሯት ያልቻሉትን ሀገራችንን ውስጣዊ አንድነታችንን በማዳከም መንግስታት ከልማት ይልቅ የእለት ችግሮቻችን ላይ ተጠመደው እንዲከርሙ በማድረግ ሀገራችን ከልማቱም ከሰላሙም እንዳትሆን ብዙ ለፍተዋል፡፡ ድህነት እና ኋላቀርነት መገለጫችን ሆኖ በአለም መድረክ እስኪነገር ኢትዮጲያ አቀርቅራ ቆይታለች፡፡
ዛሬ ግን ያ የቁዘማ ዘመን ያ በራስ ሀብት እና ፀጋ የመሸማቀቅ ታሪክ ዳግሞ ላይመለስ ተቀይሯል፡፡ ኢትዮጲያዊያን አንድነታቸውን አፅንተው፣ ከእለት ጉርሳቸው ቀንሰው ለዘመናት የህዝባችን ጥያቄ የነበረውን የመልማት ፍላጎት እና የአባይ ወንዝ እንቆቅልሽ በተባበረ ክንድ መላሽ ሰጥተዋል፡፡ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የእውነትም በህዝባችን ጥረት እና ድካም እውን ሆኗል።
ውድ ኢትዮጵያዊያን፦ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጲያ የማንሰራራት ምልክት፤ የለውጥ ጉዞ እና የታሪክ እጥፋት ጅማሮ ማብሰሪያ ነው፡፡ ግድቡ ውሃ ብቻ ሳይሆን ሉአላዊነታችን ላይ ለሚቃጡ ትንኮሳዎችም ልጓም የሚያበጅ ኃይል ነው፡፡ ኢትዮጲያዊያን እናቶች በእንጨት ለቀማ የሚደክሙት ድካም፣ የሚያባክኑት ጊዜ እና ጉልበት ከእንግዲህ አይኖርም። በኤሌክትሪክ ሀይል እጥረት ኢንዱስትሪዎቻችን ስራ አይፈቱም፣ በጋራ ተጠቃሚነት እና አብሮ የመልማት መርህ የህዳሴው ግድብ ከሀገራችን አልፎ ለጎረቤት ሀገራትም ጭምር በረከት ይዞ መጥቷል።
ውድ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ፡ ታላቁ የህዳሴ ግድብ እውን እንዲሆን ገና ከጅምሩ አንስቶ በተለያየ መልኩ ድጋፍ በማድረግ፣ በሀገር አቀፍ ሚዲያዎች ቀርባችሁ የተሳሳተ ትርክቶችን በመሞገት፣ ከእለት ጉርሳችሁ ሳይቀር ቀንሳችሁ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ እንዲሁም ህዝባዊ ንቅናቄዎችን ጭምር በማስተባበር ላበረከታችሁት አስተዋፅኦ፣ ላኖራችሁት ታሪካዊ አሻራ በራሴ እና በዩኒቨርሲቲያችን ስም እያመሰገንኩ በድጋሜ እንኳን ደስ አላችሁ እንኳን ደስ አለን እላለሁ።
ዶ/ር ኡባህ አደም

Share This News

Comment