Logo
News Photo

በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግልትን አስመልክቶ ስልጠና ተሰጠ፡፡

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ከሂጅራ ባንክ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው ስልጠና ላይ  ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም እንደገለጹት በሃገራችን የተጀመረውን ፈጣን እድገት ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ አማራጭ የፋይናንስ ተቋማትን ማስፋት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በተለይም በመስራቁ የሃገራችን ክፍል አብዛኛውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችለውን ከወለድ ነፃ የሆነ የፋይናስ አገልግሎት ተግባራዊ በማድረግ ኢንዱስትሪውን የሚደግፍ ስራዎች ሊሰፋ እንደሚገባው ጠቅሰው በዚህ ረገድም የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሚናቸው የላቀ መሆን ይገባዋል ያሉት ዶ/ር ኡባህ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲም እነዚህን አማራጭ ከወለድ ነፃ የሆኑ የፋይናንስ አገልግለቶችን በዘመናዊ መንገድ እንዲስፋፉ ለማድረግ የበኩሉን ጥረት የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን ረዳት ፕሮፌሰር ነፃነት ሽፈራው በዚሁ ስልጠና ላይ እንደገለፁት ስልጠናው አማራጭ የፋይናንስ አገልግሎቶች በምስራቁ አካባቢ ለማህበረሰቡ በስፋት መዳረስ በሚችሉበት ሁኔታን ለማመቻቸት  ዩኒቨርሲቲውም በጥናትና ምርምር የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዲችል ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰው የስልጠናው ተሳታፊዎችም ከንድፈ ሃሳብ ባለፈ ተግባራዊ እውቀት የሚቀስሙበት ስልጠና መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ለሦስት ቀን በቆየው የስልጠና መድረክ ላይ የሂጅራ ባንክ የስትራቴጂክ ማርኬቲንግ ዳይሬክተር አቶ ሙባሪክ ሸምሎ እና የባንኩ ምክትል ኃላፊ አቶ ጅብሪል  ኡስማን የተለያዩ ርዕሶች ላይ ትኩረት በማድረግ ለተሳታፊዎች ስልጠናውን የሰጡ ሲሆን ስልጠናውን ተከታትለው ላጠናቀቁ ተሳታፊዎችም የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡

በመጨረሻም የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲና ሂጅራ ባንክ በቀጣይ በጋራ ተባብረው መስራት የሚያስችላቸውን የመግባብያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡ 


Share This News

Comment