Logo
News Photo

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም የመልካም ምኞት መግለጫ

አሮጌው ዓመት አልፎ በአዲስ ሲተካ፣ የክረምቱ ዳመና እና ጭጋግ ተገፎ ሰማይ ሲፈካ፣ የተስፋ ብርሃን ሲፈነጥቅ፣ መስኩ ሲለመልም አበቦች ሲፈኩ.... ያኔ የሰው ልጅ ሐሴት ያድርጋል፣ ነገን ይናፍቃል፣ ያቅዳል፣ ተስፋን ሰንቆ ሩቅ ያማትራል.....
በመላው ዓለም የምተገኙ ኢትዮጲያዊያን፣ የሀገሬ ልጆች፣ መላው የከተማችን ድሬዳዋ ነዋሪዎች፣ የመንግስት እና የግል ተቋማት፣ ባለ ድርሻ አካላት፣ በሀገር ውስጥ እና በውጭ የምትገኙ አጋሮቻችን፣ የዩኒቨርሲቲያችን ማህበረሰብ፣ መምህራን፣ የአስተዳደር ሰራተኞች፣ የቀድሞ ምሩቃኖቻችን፣ በመላው ኢትዮጲያ የምትገኙ ውድ ተማሪዎቻችን ያቀዳችሁት እንዲሳካ፣ የናፈቃችሁት ነገ፣ የሰነቃችሁት ተስፋ እና ምኞት እውን ይሆን ዘንድ መልካም ምኞቴን እገልፃለሁ።
የዘንድሮውን አዲስ አመት ልዩ የሚያደርገው የህዳሴ ግድባችን ተመርቆ ብሩህ ተስፋን ለመላው የሀገራችን ህዝቦች መስጠት መጀመር መቻሉ ነው። ህዝባችን ያለምንም ልዩነት፣ በተባበረ ክንድ የህዳሴውን ግድብ እንዳሳካ ሁሉ ሀገራዊ አንድነቱን በማፅናት፣ የሰላሙ ዘብ በመሆን ሰላሙን በማረጋገጥ እና ሀገራችን የጀመረችውን ሁለንተናዊ የለውጥ ጉዞ በመደገፍ ሌላ ታሪክ እንደሚፅፍ፣ ከህዳሴው ግድብ ግንባታ ስኬት የማይተናነስ ሌላ ሀገራዊ ገድል እንደሚፈፅም ፅኑ እምነቴ ነው።
ውድ የዩኒቨርሲቲያችን ማህበረሰቦች፦ እንደሚታወቀው ዩኒቨርሲቲያችን የለውጥ ጎዞ ጀምሯል። በመማር ማስተማር፣ የመሰረተ ልማት ግንባታ፣ ያረጀውን የማደስ፣ የፈረሰውን መልሶ የመገንባት፣ የአሰራር ስርዓትን የማሻሻል፣ ሰፊ ማህበረሰብ ጉዳዮች ላይ የመሳተፍ፣ ተቋሙን ከመንግስት በተሰጠው ተልዕኮ እና የትኩረት መስክ መሰረት የማሸጋገር ሰፊ ስራ ተጀምሯል። የጀመርነውን ደግሞ እንደ ህዳሴ ግድባችን መላውን የተቋማችንን ሰራተኞች በማሳተፍ እውን እናደርገዋለን።
በመጨረሻም አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የጤና፣ የስኬት እና ብልጽግ እንዲሆንላችሁ፣ ያቀዳች ሁት እና ያለማችሁት ሁሉ እንዲሳካ መልካም ምኞቴን እገልጻለሁ። መልካም አዲስ ዓመት!!
ዶ/ር ኡባህ አደም
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት

Share This News

Comment