የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ከድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች ጋር የሚያቀራርብ የ’’ቃል ኪዳን ቤተሰብ’’ የተሰኘ መርሃ ግብር ተግባራዊ እንደሚሆን ተገለፀ።
የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለመከታተል ተወልደው ካደጉበት አካባቢ ወደ ተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በሚሄዱበት ወቅት ከለመዱት አካባቢ በመራቃቸው የሚፈጠርን የቤተሰብ ናፍቆት፣ ድብርት እና ብቸኝነት ለማስወገድ እንዲሁም የተማሪ ቤተሰብ በልጆቻቸው ርቆ መሄድ ስጋት እንዳይገባቸው እና ተማሪዎች ከአካባቢው ማህበረሰቡ ጋር ተቀራርበው እና የቃል ኪዳን ቤተሰብ መስርተው እንዲቆዩ ለማስቻል የ ‘’ቃል ኪዳን ቤተሰብ’’ የተሰኘ መርሃ ግብር ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገለፀ። የ’’ቃል ኪዳን ቤተሰብ’’ የተሰኘውን ፕሮግራም ማስጀመር ይቻል ዘንድ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላቶች ጋር ውይይት አድርጓል። የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር እና ልማት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሰለሞን ዘሪሁን በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ‘’ ተማሪን ከማህበረሰቡ ጋር ማቀራረብ እንዲሁም ቤተሰባዊ ትስስር መፍጠር ተማሪዎች በትምህርታቸ እንዲበረቱ እና ውጤታማ እንዲሆኑ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል’’ ብለዋል። ‘’የቃል ኪዳን ቤተሰብ’’ ተማሪ እና ማህበረሰቡን ከማቀራርብ ባሻገር የማህበረሰብ ትስስርን ለመፍጠር እና የመረዳዳት ባህልን ለማጎልበት ከፍተኛ አበርክቶ ይኖረዋል ያሉት ዶ/ር ሰለሞን የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ይህንን ሀገራዊ እና አካባቢያዊ ፋይዳው የጎላ መርሃ ግብር በማስጀመር ሰፊ ስራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ፍትህ፣ ፀጥታና ህግ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱሰላም አህመድ በበኩላቸው ‘’ድሬዳዋ የሰላም፣ የፍቅር እና የአብሮነት ከተማ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ የቃል-ኪዳን ቤተሰብ መመስረቱ ወደ ድሬዳዋ የሚመጡ ተማሪዎች በይበልጥ የድሬን ባህል እና የአኗኗር ዘይቤ እንዲያውቁ እንደሚረዳና ይህም በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እና በአካባቢው ማኅበረሰብ መካከል ያለውን ግንኙነት ያጠናክራል’’ ብለዋል።
አቶ አብዱሰላም አያይዘውም የቃል-ኪዳን ቤተሰብ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በትምህርታቸው እንዲጠነክሩ ከማገዝ ባሻገር አብሮነትንና የእርስ በእርስ የባህል ትስስር እዲጎለብት ሚናው የጎላ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ‘’የቃል ኪዳን ቤተሰብ’’ የተሰኘውን መርሃ ግብር ከ 2018 ዓ/ም የትምህርት ዘመን ጀምሮ ተግባራዊ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል።
Share This News