በድሬ ዳዋ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የስርዓተ ትምህርት ልማት እና ክለሳ ስልጠና ተካሄደ፡፡
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የአካዳሚክ ፕሮግራሞችን ጥራትና አግባብነት ለማሳደግ ያለመ የአንድ ቀን የስርዓተ ትምህርት ልማትና ክለሳ ስልጠና በተሳካ ሁኔታ አካሄደ። ስልጠናው የስርዓተ ትምህርት ኦዲትና የስርዓተ ትምህርት ልማት ኮሚቴ አባላትን ያካተተ ሲሆን ከ90 በላይ የአካዳሚክ ባለሙያዎች የተሳተፉበት ነበር።
የድሬ ዳዋ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ካሉ 15 የተግባር ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎች (Applied Science University) አንዱ እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን፣ ሀገራዊ የልማት ፍላጎቶችን የሚያሟላ ተግባራዊ፣ ኢንዱስትሪ-ተኮር ትምህርትን ለማረጋገጥ ስርአተ ትምህርቱን ከተግባራዊ ሳይንስ-ተኮር አካሄድ ጋር ለማጣጣም የስርዓተ ትምህርት ክለሳና ዝግጅት እያከናወነ ይገኛል፡፡
በመክፈቻው ፕሮግራሙ ላይ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንትፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ግርማ ቤካ ባስተላለፉት መልዕክት ቀጣይነት ያለው የስርዓተ ትምህርት ግምገማና ልማት ስላለው ጠቀሜታ አበረታች መልእክት አስተላልፈዋል። ጠንካራ፣ በሚገባ የተዋቀረ እና የተሻሻለ ስርዓተ ትምህርት ብቁ መሃንዲሶችን እና የቴክኖሎጂ ባለሙያዎችን ለማፍራት መሰረት መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል። ዳይሬክተሩ በተጨማሪም ስርዓተ ትምህርቱ ለወቅታዊ የቴክኖሎጂ እና የኢንዱስትሪ እድገቶች የበለጠ ምላሽ ለመስጠት በአካዳሚክ ሰራተኞች መካከል የቡድን ስራ፣ ፈጠራ እና ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።’’
ስልጠናው በድሬ ዳዋ ዩኒቨርሲቲ ቴክሎጂ ኢንስቲትዩት አዘጋጅነት የተሰጠ ሲሆን በስርዓተ ትምህርት ፅንሰ-ሀሳቦች እና የስርዓተ ትምህርት ቀረጻ፣ ክለሳ እና አተገባበር ላይ ያተኮረ ነው። ተሳታፊዎቹ ስርዓተ ትምህርቶች የተግባር ሳይንስ መርሆዎችን ውህደት ማጠናከር፣ የኮርሶች አሰጣጥን ማሻሻል እና መርሃ ግብሮች ለስራ ገበያ ፍላጎቶች ምላሽ ሰጪ መሆናቸውን ማረጋገጥ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል።
Share This News