Logo
News Photo

ሁለተኛው ዙር የኮቪድ 19 የመከላከያ ክትባት ዘመቻ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ተጀመረ፡፡

የክትባት ዘመቻውን በዛሬው እለት በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በመገኘት በይፋ ያስጀመሩት የድሬዳዋ አስተዳደር ንግድ፣ ኢንደስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀርቢ ቡህ እንዳስታወቁት የኮቪድ 19 ወረርሺኝ በሀገራችን ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ እስካሁኗ ሰከንድ ድርስ በርካታ ወገኖቻችንን በሞት እየነጠቀን እና ለከፋ ህመም እየዳረጋቸው እንደሆነ ገልፀዋል።

በተለይም ወረርሺኙ እያስከተለ ባለው የጤና ችግር ሳቢያ በአስተዳደራችን ድሬደዋ ከፍተኛ የሆነ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና እያስከተለ ይገኛል ያሉት አቶ ሀርቢ የኮሮና ወረርሺኝ ለመከላከል እድሚያቸው ከ12 ዓመት በላይ የሆኑ መላው የአስተዳደራችን ነዋሪዎች የመከላከያ ክትባቱን በመከተብ  የበኩላቸውን ግዴታ መወጣት ይኖርባቸቸዋል ሲሉ አስገልዝበዋል፡፡

የድሬደዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ለምለም በዛብህ በበኩላቸው እስካሁን በአስተዳደራችን ድሬደዋ ቁጥሩ ከ80 ሺህ በላይ የሆ ሰውን መከተብ መቻሉን ገልፀው በዛሬው እለትም በሚጀመረው ሁለተኛው ዙር  ዘመቻ 100 ሺህ ለሚሆኑ የአስተዳደራችን ነዋሪዎች የመከላከያ ከትባቱን ተደራሽ ለማድረግ መታቀዱን ተናግረዋል።

ዛሬ በተጀመረው ዘመቻ እድሜያቸው ከ12 ዓመት በላይ የሆኑ የአስተዳደራችን ነዋሪዎች መከተብ አለባቸው ያሉት ኃላፊዋ ከዚህ በፊት ከትባቱን የወሰዱና ከዚህ ቀደም ክትባቱን ያልወሰዱ ነዋሪዎች እንዲሁም 6 ወር የሆናቸው ነዋሪዎችም የማጠናከሪያ ክትባቱን መውሰድ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዘዳንትና የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ተወካይ ዶ/ር መገርሳ ቃሲም በዚሁ የክትባት ዘመቻ ማስጀመሪያ ስነ-ስርዓት ላይ ተገኝተው እንዳሉት የዩኒቨርሲቲው መምህራን፣ ተማሪዎች እና የአስተዳደር ሠራተኞች የኮቪድ 19 የመከላከያ ክትባቱን በመውሰድ ወረርሺኙ ሊያስከትል ከሚችለው ጉዳት ራሳቸውን መጠበቅ ይኖርባቸዋል በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ 

ዛሬ በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ በተጀመረው የክትባት ዘመቻ ላይ የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ የሃገራችን አርቲስቶችና የዩኒቨርሲቲው መላው ማህበረሰብ የኮቪድ 19 መከላከያ ክትባቱን ተከትበዋል፡፡ 


Share This News

Comment