ውስጣዊ አቅምን በመጠቀም የተገነባ ዘመናዊ የምግብ ማብሰያ ስፍራ ተመረቀ
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ውስጣዊ አቅምን በመጠቀም ዘመናዊ እና ምቹ የምግብ ማብሰያ፣ ማቀነባበሪያ እና ማቆያ ስፍራዎችን እየገነባ ይገኛል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለግንባታ ስራ ከሚበጅተው ዓመታዊ በጀት ውጪ አገልገሎታቸውን የጨረሱ እና የወዳደቁ ቁሳቁሶችን በመጠቀም ዘመናዊ የምግብ ማብሰያ ስፍራዎችን በመገንባት ዩኒቨርሲቲው የሚሰጠውን አገልግሎት የማዘመን ስራ እየሰራ ይገኛል፡፡
የምግብ ማብሰያ ስፍራ መርቀው የከፈቱት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም ባስተላለፉት መልዕክት ዛሬ ለምርቃት የበቃው የምግብ ማብሰያ ስፍራ ዩኒቨርሲቲውን ለሰራተኞች ምቹ የማድረግ፣ ተቋሙ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ጥራት የማሻሻል እንዲሁም የተቋሙን መለካምድራዊ ገፅታ የማስዋብ ስራ አንዱ አካል ምሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ኡባህ አደም አክለውም ቀድሞ የነበረው የመስሪያ ቦታ ለእንጀራ ጋጋሪ እናቶች እንዲሁም ሰራተኞች ምቹ ካለመሆኑም በላይ ዩኒቨርሲቲው ለተማሪዎች በሚሰጠው አገልገሎቶች ጥራት ላይም አሉታዊ ሚና የነበረው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ግንባታው የተሰራበትን ሂደት ያብራሩት የአስተዳደር እና ልማት ም/ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር ሰለሞን ዘሪሁን በበኩላቸው ‘’ከግንባታ ዲዛይን፣ ግንባታ ስራ፣ የኤሌክትሪክ ስራ እንዲሁም በር እና መስኮት ምርት እና ገጠማ ሰራዎች በዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች ተሰርቷል’’ ብለዋል፡፡ በውስጥ አቅም የሚሰሩ ስራዎች በኮንትራት ከሚሰሩ ፕሮጀክቶች ይልቅ ውጣ ውረድ እንደሚበዛባቸው የጠሙት ምክትል ፕሬዝዳነቱ በሰራተኞች ርብርብ እና በከፍተኛ አመራሩ እገዛ ለስኬት መብቃታቸውን ተናግረዋል፡፡
በግንባታ ስራው ላይ ለተሳተፉ ሰራተኞች እና በየደረጃው ለስራው ስኬት አስተዋፅኦ ላደረጉ አመራሮች እውቅና ተሰጥቷል፡፡
Share This News