Logo
News Photo

የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት ለተለየው የኦሮምኛ አርቲስት ለኑሆ ጎበና የማስታወሻ ፕሮግራም አዘጋጀ፡፡

የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ከአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ትምህርት ክፍል ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የማስታወሻ ፕሮግራም ላይ የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባን በመወከል ንግግር ያደረጉት አቶ ካሊድ መሐመድ ኑሆ ጎበና እድሜ ዘመኑን ሙሉ ለተጨቆኑና ለተገፋ ህዝቦች በሙዚቃዎቹ ድምፁን ሲያሰማ የነበረ ታላቅ አርቲስት ነው፥ ዩኒቨርሲቲውም ይህ ታላቅ አርቲስት ለነጻነትና ለሰው ልጆች መብት መጠበቅ ያደረገውን ተጋድሎ ከግምት ውስጥ በማስገባት በዚህ መልኩ አርቲስቱን ማሰብ ሊያስመሰግነው እና ሌሎችም በአርያነት ሊከተሉት የሚገባ ነው ብለዋል፡፡ 

በዚሁ የማስታወሻ ፕሮግራም ላይ የተገኙት የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ተወካይ ዶ/ር መገርሳ ቃሲም በበኩላቸው የድሬደዋ ከተማ ለኦሮምኛ ባህልና ቋንቋ እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከት የቻሉ አርቲስቶችን ያፈራች ከተማ ስትሆን ከእነዚህ አርቲስቶች መካከልም ኑሆ ጎበና ከግንባር ቀደሞቹ ተርታ የሚሰለፍ አርቲስት  ነው ብለዋል፡፡

አርቲስት ኑሆ ጎበና እድሜ ዘመኑ  በሙዚቃዎቹ ስለ ነፃነት፣ ስለ አንድነት፣ ስለ ሰላም እና ሰለ ሃገር በማቀንቀን ለሰው ልጆች እኩልነት ሙሉ ህይወቱን የሰጠ ታላቅ አርቲስት ነው ያሉት ዶ/ር መገርሳ ዩኒቨርሲቲው የዚህ ታላቅ አርቲስት ስራዎች ላይ በቀጣይ ጥናትና ምርምር በማካሄድ ስራዎቹ ለእዲሱ ትውልድ እንዲተላለፍ የተለያዩ ተግባራት ይከናወናሉ ብለዋል፡፡

የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የምርመርና ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሰለሞን ዘሪሁንም ለዚህ ታላቅ አርቲስት በዘላቂነት ማስታወሻ ሊሆኑ የሚችሉ ተግባራት በዩኒቨርስቲው በኩል እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል፡፡

በዚሁ የማስታወሻ ፕሮግራም ላይ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በተጋባዥ እንግድነት የመጡት ዶ/ር አሸናፊ በላይ የአርቲስቱን ህይወትና ስራዎቹን የተመለከተ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡ ሲሆን የአርቲስቱ ባለቤት ወ/ሮ መሊካ እንዲሁም ታዋቂዎቹ አርቲስቶች ሸንተም ቹቢሳ፣ ኤሌሞ አሊ እና መሀመድ ቆጴ በመድረኩ ላይ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡   

 

Share This News

Comment