ግምቱ 1.2 ሚሊየን ብር የሚሆን የትምህርት ቤት ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደረገ
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ለጀልዴሳ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ት/ርት ቤት 1.2 ሚሊየን ብር ዋጋ ያላቸው የትምህርት ቤት ቁሳቁሶችን ድጋፍ አደረገ፡፡ ድጋፍ የተደረጉት የትምህርት ቤት ቁሳቁሶች 57 የተማሪ መማሪያ ዴስክ፣ 100 የመቀመጫ ወንበር እና 50 የመመገቢያ ጠረጴዛ መሆናቸውን ማወቅ ተችሏል፡፡
ድጋፉን አስመልክቶ በተሰናዳ የርክክብ መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተማም አወል እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው አንገብጋቢ የማህበረሰብ ችግሮችን በመለየት የተለያዩ ድጋፎችን እንደሚያደርግ በመጠቆም በተለይ የውስጥ አቅምን በመጠቀም የሚደረጉ ድጋፎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥሉበት አስገንዝበዋል፡፡
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ያሉትን ምሁራን እውቅት እና ውስን ሀብት በመጠቀም አንገብጋቢ የማህበረሰቡን ችግሮች ለመፍታት ሰፊ ስራ እየሰራ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ተማም በተለይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ሰፊ ማህበረሰብ አቀፍ ስራዎችን ለመስራት ዝግጁ ስለመሆናቸውም ተናግረዋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አቡበከር አብዶሽ በበኩላቸው የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በሚሰራቸው ማህበረሰብ አቅፍ ስራዎች ለሌሎች ተቋማትም ትልቅ አርአያ እየሆነ ነው ያሉ ሲሆን ‘’ድጋፉ በትምህርት ቤቱ የነበረውን የቁሳቁስ እጥረት በመቅረፍ ተማሪዎች በትምህርታቸው ላይ በተሻለ ሁኔታ እንዲያተኩሩ ያስችላቸዋል’’ ብለዋል፡፡
በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሜካኒካል ምህንድስና መምህራን እና ረዳት ቴክኒሲያኖች ቁሳቆሶቹን በማምረት ሂደት ውስጥ ላደረጉት ከፍተኛ አተዋፅኦ የምስጋና ምስክር ወረቅተ ተሰቷቸዋል፡፡
Share This News