ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ለአስተዳደሩ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ 3 የማማከር ስራ ፕሮጀክቶችን ለመስራት ተስማማ።
ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ባለፉት ዓመታት ከአስተዳደሩ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ጋር ሰርቶ ባስረከበው የአምራች ኢንዱስትሪዎች የ10 ዓመታት ፍኖተ ካርታን ለማስተግበር የሚረዱ 3 አዳዲስ የማማከር ስራ ፕሮጀክቶችን ለመስራት ተስማምቷል።
በስምምነት መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ቴክኖሎጅ ሽግግር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተማም አወል ቢሮው ዩኒቨርስቲያችን ካሉት ቁልፍ አጋሮች ቀዳሚው መሆኑን ጠቅሰው የጋራ ሃገራዊ ተልእኳችንን ለማሳካት ከዚህም የበለጠ መስራት ይጠበቅብናል የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል። በሌላ በኩል ከኢንዱስትሪው ጋር በቅርበት ብቻ ሳይሆን አንድ ላይ መስራት ለሁለቱም ተቋማት ፋይዳው የጎላ መሆኑን የተቆሙት ዶ/ር ተማም ዛሬ የተፈረሙት ፕሮጀክቶች ያላቸውን ተቋማዊ፡ ቀጠናዊና ሀገራዊ ጉልህ ድርሻ አብራርተዋል።
የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ም/ሃላፊ አቶ አብዲ ሙክታር በበኩላቸው ዩኒቨርስቲው በትጋትና ቁርጠኝት እየሰራ ያለውን ስራ አድንቀው ኢንዱስትሪውን በጋራ ደግፈን ለአስተዳደራችንም ለሃገራችንም ከኢንደስትሪው የሚጠበቀውን የልማት ውጤት ማሳየት አለብን ብለዋል።
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጅ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር እሸቱ መኮንን በበኩላቸው ከዚህ ቀደም በሰራናቸው የጋራ ፕሮጀክቶቻችን እንዳደረግነው ሁሉ አሁንም ከቢሮው ጋር የተፈራረምናቸው 3ቱ ፕሮጀክቶች በጥራትና በፍጥነት እንዲጠናቀቁ የክትትል ስራውን በጥብቅ ዲሲፕሊን እንደሚወጣ ተናግረዋል።
Share This News