የዩኒቨርሲቲውን ሠራተኞች የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ የሚያደርግ የጋራ መግባቢያ ስምምነት ተፈረመ፡፡
የጋራ የመግባቢያ ስምምነቱ በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ እና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ድሬዳዋ ዲስትሪክት መካከል የተደረገ ነው፡፡ ባንኩ ባለፈው ህዳር 02 ቀን 2018 ዓ.ም የሲቢኢ በእጄ ዲጂታል የቁጠባ እና የብድር አገልግሎት መተግበሪያን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ በዚሁ መሰረት ደመወዛቸውን በሲቢኢ ብር የሚቀበሉ የዩኒቨርሲቲው መምህራን እና የአስተዳደር ሰራተኞች የብድር አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበት እድል ተመቻችቷል፡፡
በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ወቅት የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም ባስተላለፉት መልዕክት ‘’ሰራተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የባንክ አገልግሎትን ከማስተዋወቅ አንጻር የኢትዮጲያ ንግድ ባንክ ይዞት የመጣው አሰራር የሚበረታታ ነው ያሉ ሲሆን የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ለስምምነቱ ተፈጻሚነት በቁርጠኝነት ይሰራል’’ ብለዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከሦስት ሺህ በላይ ሰራተኞች እንዳሉት ያስታወሱት ዶ/ር ኡባህ የቀረበው የብድር አገልግሎት አማራጭ የሰራተኛውን ኑሮ ከማገዙም በላይ የስራ ተነሳሽነት እና እርካታ ከመጨመር አንጻር አውንታዊ ተጽዕኖ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የድሬዳዋ ዲስትሪክት ኃላፊ አቶ ገዛኽኝ በቃና በበኩላቸው የጋራ ስምምንቱ ባንካቸው ከዩኒቨርሲቲው ጋር ያለውን የቆየ ግንኙነት የበለጠ ያጠናክረዋል ያሉ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ አገልግሎቱን በተመለከተም በቀጣይ በቂ የሆነ ግንዛቤም እንደሚፈጠር አቶ ገዛኽኝ አስገንዝበዋል።
Share This News