Logo
News Photo

126 ኛው የአደዋ የድል በዓል "ዓድዋ የኢትዮጵያ እና የጥቁር ህዝቦች የሉአላዊነት መገለጫ" በሚል ርዕስ በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ በፓናል ውይይት ተከበረ፡፡

በፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎችን እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ንግግር ያደረጉት በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሰለሞን ዘሪሁን እንደገለጹት የአደዋ ድል ለእኛ ለኢትዮጵያኖች ብቻ ሳይሆን ለመላው የጥቁር ህዝቦች ኩራት መሆኑን በንግግራቸው አንስተዋል።

ይህን የትናንት ገድላችን ወኔ ሆኖን ዛሬ ላይ የተሻለ ስራ መስራት እንድንችል ታሪክን መማርና ማወቅ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ የፓናል ውይይቱ ሊዘጋጅ መቻሉን ዶ/ር ሰለሞን ገልፀው የዩኒቨርሲቲው የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል ለመጀመሪያ ጊዜ በሙሉ ባለቤትነት የዚህ አይነቱን ትልቅ ዝግጅት ማሰናዳት መቻሉ የሚበረታታና በዩኒቨርሲቲው የሚገኙት ሌሎች የትምህርት ክፍሎችም በአርያነት ሊከተሉት የሚገባ ተግባር ነው ብለዋል፡፡

አባቶቻችን በእብሪት ተነስቶ ሃገራችንን ለመውረር የመጣውን ቀኝ ገዢ ኃይል ከፍተኛ መስዋትነት ከፍለው የዓለምን ታሪክ መቀየር እንደቻሉት ሁሉ እኛ ልጆቻቸውም ልዩነቶቻችንን አቻችለን በአንድነት ከፊታችን የተጋረጠብንን ችግር በድል መወጣት ይገባናል ያሉት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም በተለይም በዘመናችን የሀገራችን ቀንድኛ ጠላት የሆኑትን ድህነትና ኋላቀርነት ላይ የተባበረ ክንዳችን በማሳረፍ የህዝባችን ኑሮ እንዲሻሻል ሁላችንም በተሰማራንበት መስክ ውጤታማ ስራ በመስራት የሚጠበቅብንን እንወጣ ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡ 

126 ኛውን የአደዋ ድል በአል ምክንያት በማድረግ የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር የትምህርት ክፍል ከማህበረሰብ አገልግልት ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ " ሥነ-ጽሁፋዊ ምሰላና ድምፅ አልባዎቹ የዓድዋ ድል ባለቤቶች" እና "የአድዋ ጦርነትና ለቱሪዝም ሃብትነት ያለው አቅም "  የሚል ርዕስ ያላቸው ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ 

በመጨረሻም የአደዋን ድልን የሚዘክር የኪነ- ጥበብ ዝግጅት በድሬደዋ ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት በሚሊንየም የባህልና የኪነጥበብ ቡድን ቀርቧል፡፡  

Share This News

Comment