Logo
News Photo

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ፕሮግራሞች ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኙ እሰራለው አለ

ዩኒቨርሲቲው የሚሰጣቸው የትምህርት ፕሮግራሞች ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ እና እውቅናም እንዲያገኙ የሚሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡ የዚሁ እቅድ አካል የሆነው እና የአንስቴዢያ ትምህርት ክፍል ሀገር አቀፍ የጥራት ደረጃ እውቅና እንዲሰጠው የሚያስችል መርሃ ግብር ዛሬ ተካሂዷል፡፡

የትምህርት እና ስልጠና ባለስልጣን ባለሙያዎች የአንስቴዢያ ትምህርት ክፍል ሀገራዊ ጥራት ስለማሟላቱ የመስክ ምልከታ እና ግምገማ ለማድረግ በተገኙበት መርሃ ግብር ላይ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ 

ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራትን ከማሻሻል እንዲሁም ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን ብቁ የተማረ የሰው ሃይል ከማሰልጠን አኳያ የተቃኙ እንዲሁም ዘመኑን የሚዋጁ የትምህርት ፕሮግራሞችን ተደራሽ የማድረግ ድርብ ሃላፊነት አለባቸው ያሉት ዶ/ር ኡባህ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲም የተሰጠውን ሀገራዊ ተልዕኮ ከግብ ለማድረስ እየሰራ ስለመሆኑ አመላክተዋል፡፡ 

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም አክለውም ‘’በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የሚገኙ ት/ርት ክፍሎች እራሳቸውን በመፈተሽ እና በሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ደረጃ የተመለከቱ የጥራት መስፈርቶችን ባገናዘበ መልኩ እራሳቸውን በማደራጀት እውቅና ለማግኘት መስራት ይኖርባቸዋል’’ ያሉ ሲሆን ዩኒቨርሲቲው ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ስራዎችን ለመገምገም እና የመስክ ምልከታ ለማድረግ ለመጡ የባለስልጣኑ ልኡካን የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት እና ምስጋና አቅርበዋል፡፡

Share This News

Comment