Logo
News Photo

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ የተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በመምከር ውሳኔዎችን አስተላለፈ

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ ስብሰባ የዩኒቨርሲቲውን የስድስት ወር የስራ አፈፃፀም ሪፓርት ጨምሮ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ እና ውሳኔዎችን በማስተላለፍ ተጠናቀቀ፡፡ 

ስራ አመራር ቦርዱ ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ስድስት ወራት የከወናቸው ተልዕኮ ተኮር ስራዎች መልካም አፈፃፀም ያሳዩ መሆኑን በመገምገም በቀጣይነት ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰሩ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ምክረ ሃሳብ ሰጥቷል፡፡ ቦርዱ በሌላ በኩል አዲሱን መዋቅር  በሚመለከት የቀረበ ሪፓርት፣ ተልዕኮ እና ትኩረት መስክ ልየታ የስራ አፈፃፀም፣ የልህቀት ማእከላትን በሚመለከት የቀረበ የአመራር ምደባ፣ የአርት ት/ርት ቤትን ለማስጀመር የቀረበ ረቂቅ ሰነድ ቀርበውለት ተወያይቷል፡፡ 

በተለይ የአሊ ቢራ አርት ት/ርት ቤትን ለማቋቋም የቀረበውን ረቂቅ ሰነድ የገመገመው የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የስራ አመራር ቦርድ ክቡር አርቲስት አሊ ቢራ በሙዚቃ ኪነ ጥበብ ዘርፍ ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋፅኦ፣ በምስራቁ የሀገራችን ክፍል ለረዥም ዘመናት የዘለቀ የኪነጥበብ ፍቅር እና አካባቢያዊ ፀጋ እንዲሁም በዘርፉ ያለውን የሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረት ታሳቢ ባደረገ መልኩ ትምህርት ቤቱ እንዲከፈት ውሳኔ አሳልፏል፡፡ 

ቦርዱ የሀብት ማፈላለግ ስራዎችን በተመለከተም ውይይት ያደረገ ሲሆን ጅምር ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ 

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ስድስት ወራት በተቋም ደረጃ የተሰሩ ስራዎች አበረታች መሆናቸውን በመጠቆም ለተሸለ ተቋማዊ ስኬት ሁሉም የዩኒቨርሲቲው አመራር እንዲሁም ሰራተኛ ከመቼውም ጊዜ በላቀ መልኩ አንዲተጋ በማሳሰብ ስብሰባውን አጠናቋል፡፡

Share This News

Comment