Logo
News Photo

ዘመናዊ የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓትን በመዘርጋት ለነዋሪዎቿ ምቹ የሆነች ውብና ፅዱ ድሬደዋን እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበኩሉን እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆኑን የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ፡፡

የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ከድሬደዋ አስተዳደር ፅዳትና ውበት ኤጀንሲ ጋር በመተባበር "የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ አሠራሮች እና በዘርፉ የግል ኢንቨስትመንት አዋጪነት" በሚል ርዕስ ለአንድ ቀን የቆየ ጥናታዊ የውይይት መድረክን ተካሂዷል፡፡

የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሰለሞን ዘሪሁን በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ዘመናዊ የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓትን በመዘርጋት ለነዋሪዎቿ ምቹ የሆነች ውብና ፅዱ ድሬደዋን እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበኩሉን እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በዛሬው እለትም የሚቀርበው የምርምር ስራም የዚሁ እንቅስቃሲያችን አንድ አካል ነው ያሉት ዶ/ር ሰለሞን በወረቀት ላይ የሰፈሩትን የምርምር ስራዎች ወደ ተግባር በመቀየር የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድን በዘመናዊ መንገድ በማስተዳደር የማህበረሰቡን ችግር በዘላቂነት መፍታት እንደሚገባ ገልጸው ሁሉም አካል የበኩሉን ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በዚሁ መድረክ  ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የድሬደዋ አስተዳደር ፅዳትና ውበት ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ሀቢብ ፋራ እንደገለጹት በድሬደዋ ከተማ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚመነጨው ደረቅ ቆሻሻ በአይነትም ሆነ በመጠን እየጨመረ የመጣ ቢሆንም ይህንን ደረቅ ቆሻሻ በአግባቡ ከማስተዳደር አኳያ ሰፊ ክፍተት በመኖሩ ከተማዋን ለከፋ የፅዳት መጓደል ዳርጓት ይገኛል ብለዋል፡፡ 

የደረቅ ቆሻሻን በአግባቡ ማስተዳደር አለመቻል ዋነኛ ምክንያት ደግሞ ይህንን አገልግሎት የሚሰጡ አካላት አቅም ማነስ፣ የዘመነ አሰራር አለመኖር እና የህብረተሰቡ እና የባለድረሻ አካላት ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆን ናቸው ያሉት አቶ ሀቢብ እነዚህን ችግሮች በጥልቀት በመመርመር በቀጣይ ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት የሚችል ስራ ከድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ኤጀንሲያቸው ከ2013 በጀት ዓመት ጀምሮ ሲያከናውን መቆየቱን ጠቁመው የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድን ዘመናዊ ለማድረግ የተጀመረው ስራም ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ገልፀዋል፡፡

"የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ አሠራሮች እና በዘርፉ የግል ኢንቨስትመንት አዋጪነት" በሚል ርዕስ ለአንድ ቀን በቆየው የውይይት መድረክ ላይ የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን እና ተመራማሪዎች ዘመናዊ የደረቅ ቆሻሻን አስመልክቶ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች አቅርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡  

Share This News

Comment