Logo
News Photo

የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ በድሬዳዋ ለሚገኙ 12 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተለያዩ ማጣቀሻ መጽሐፍትና የሴት ተማሪዎች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ፡፡

የድሬደዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ የተከበሩ ወ/ሮ ሙሉካ መሐመድ በመፅሐፍ ርክክብ ሥነ-ስርዓት ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ለትምህርት ቤቶች አስተዳደሩ በትምህርቱ ዘርፍ የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ እያደረገ ያለው ጥረት የሚያግዝና ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን በመግለፅ ዩኒቨርሲቲው ላደረገው ድጋፍ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበው ወደፊትም የሚያደርገውን ፈርጀ-ብዙ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡ 

በዩኒቨርሲቲው የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሰለሞን ዘሪሁን በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በተለይም በሳይንስና በሒሳብ ትምህርት የተሻለ ውጤት ያላቸውን የ1ኛ እና የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በንድፈ-ሀሳብ የቀሰሙትን  እውቀት  በተግባር ልምምድ የሚያዳብሩበት ሁኔታ በማመቻቸት ነገ ከራሳቸው አልፈው ሀገራቸውን መጥቀም የሚችሉ ዜጎችን ለመፍጠር የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ 

ዶ/ር ሰለሞን አያይዘውም ዩኒቨርሲቲው እያደረገ ያለው ድጋፍ ግቡን እንዲመታ ትምህርት ቢሮ፤ ትምህርት ቤቶች፣ መምህራን እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በሙሉ ከዩኒቨርሲተው ጋር ከቀድሞ በበለጠ ተቀራርበው ይሰሩ ዘንድ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ወንዲፍራው ደጀኔ በበኩላቸው የመፅኀፍቱ ድጋፍ የተደረገላቸው 12 ትምህርት ቤቶች መሆኑን ገልፀው በድምሩ 1,747 (አንድ ሺህ ሰባት መቶ አርባ ሰባት) የሂሳብ፣ ባዮሎጂ፤ ኬሚስትሪና ፊዚክስ የትምህርት ዓይነቶች ማጣቀሻ መፅሃፍት ድጋፍ መደረጉን ተናግረው ድጋፉ የተደረገላቸው ትምህርት ቤቶች የተመረጡትም ዩኒቨርሰቲው በሚሰጠው የሳ.ቴ.ም.ሂ (STEM) ፕሮግራምና የሳይንስ ጥያቄና መልስ ውድድር (Science Olympiads) ላይ ባላቸው ተሳትፎ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ 

በተጨማሪም ዶ/ር ወንዲፍራው እንደገለፁት በእለቱ ድጋፍ ከተደረገላቸው ትምህርት ቤቶች በተጨማሪ ከድሬ ዳዋ ገጠር ቀበሌዎች ተውጣተው የድሬዳዋ ትምህርት ቢሮ ባዘጋጀው ሆስቴል ውስጥ አየኖሩ ለሚማሩ ሴት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የመፅፍት ድጋፍ ከማድረግም በተጨማሪ ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በተሰበሰበ ከ24 ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዛ ለ95 ሴት ተማሪዎች ለ1 ዓመት ከ6 ወር የሚያገለግል የንፅህና መጠበቂያ ድጋፍ መደረጉን ገልፀው በለጋስነት ላደረጉት ድጋፍ የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ አመስግነዋል፡፡ 


Share This News

Comment