Logo
News Photo

የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ በህክምና ጤና ሳይንስ ትምህርት በቅድመ ምረቃ ሲያስተምራቸው የነበሩ 82 ተማሪዎችን ዛሬ አስመረቀ፡፡

በምረቃው ስነ-ስርዓት ላይ በመገኘት ለተመራቂ ተማሪዎችና ለተመራቂ ቤተሰቦች የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት ያስተላለፋ በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንትና የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ተወካይ ዶ/ር ሰለሞን ዘሪሁን ናችው፡፡

ዶ/ር ሰለሞን በዚሁ ወቅት እንዳሉት የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በዛሬው እለት በመጀመሪያ ዲግሪ ያስመረቃቸው ተማሪዎች በሚድዋይፈሪ  54 በአንስቴዢያ 14 እና በፋሚሊ ሄልዝ 14 በድምሩ 82 ተማሪዎችን አስመርቋል ብለዋል፡፡ 

ከአጠቃላይ ተመራቂዎች መካከል 42 ሴቶች ናቸው ያሉት ዶ/ር ሰለሞን በጤናው የትምህርት ዘርፍ ላይ የሴቶች ተሳትፎ  ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱ ይበል የሚያሰኝ  ለውጥ መሆኑን ገልጸው የህክምና ጤና ሳይነስ ኮሌጅ በጤናው ዘርፍ ብቁና የሰለጠነ የሰው ኃይል ከማፍራት ጎን ለጎን በድሬደዋ አስተዳደር የጤና አገልግሎት ሽፋን በስፋትና በጥራት ወደ ማህበረሰቡ እንዲደርስ የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ተማሪዎች በተለያዩ ጥናቶችና የማህበረሰብ አገልግሎቶች ላይ በመሳተፍ እያደረጉት ያለው አስተዋፅኦ ተጠቃሽ ነው ብለዋል፡፡

በዚሁ የምረቃ ስነ-ስረዓት ላይ በመገኘት ንግር ያደረጉት የእለቱ የክብር እንግዳ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የአከዳሚክ ጉዳዮች ጀነራል ዳይሬክተር ክቡር ዶ/ር ኤባ ሚጀና እንዳስታወቁት ተመራቂዎች ትምህርት ማጠናቀቅ የመጨረሻ ግብ አለመሆኑን አውቃችሁ የዛሬዋ እለት ለበለጠ ኃላፊነት የምትዘጋጁበትና ራሳችሁን፣ ቤተሰባችሁንና ሀገራችሁን የሚጠቅም ተግባር ለመፈፀም ዝግጁ የምትሆኑበትና ወደ ላቀ ተግባር ለመሸጋገር ቃል የምትገቡበት ዕለት በመሆኑ ይህንኑ አውቃችሁ የተጣለባችሁን አደራ መወጣት ይኖርባቹሃል በማለት አስገንዝበዋል፡፡ 

በዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር መገርሳ ቃሲም በበኩላቸው ተመራቂ ተማሪዎች ሞያው የሚጠይቀውን ስነ-ምግባር አክብረው ጤናው የተጠበቀ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት ይሳካ ዘንድ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ላመጡና በማህበረሰብ አገልግሎት የተሻለ ተሳትፎ ለነበራቸው ተማሪዎች የሚዳሊያና የምስክር ወረቀት ከእለቱ የክብር እንግዶች እጅ ተረክበዋል፡፡ 


Share This News

Comment