Logo
News Photo

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የመምህራን ማህበርን በአዲስ መልክ ለማዋቀር የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴዎች ምርጫ ተካሄደ፡፡

የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲን የመምህራን ማህበርን በአዲስ መልክ ለማዋቀር በተጠራው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ከሁሉም የትምህርት ክፍል የተወጣጡ ተወካዮች የተሳታፊ የሆኑበት ሲሆን በዚሁ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ማህበሩን ለቀጣይ ሶስት ዓመታት የሚመሩ 7 አባላት ያሉት የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ምርጫም ተደርጓል፡፡

በዚሁ ጉባዔ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገለግሎት ም/ፕሬዝዳንትና የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ተወካይ ዶ/ር ሰለሞን ዘሪሁን እንደገለፁት በዩኒቨርሲቲው ጠንካራና ከባድ ኃላፊነትን መሸከም የሚቸል የመምህራን ማህበር መኖር መምህራን የሚያነሷቸው ጥያቄዎች አፋጣኝና ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኙ በማድረግ የመምህራን መብትና ጥቅማ ጥቅም እንዲከበር ያደርጋል ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራርም ለመምህራን ማህበሩ እገዛና ድጋፍ በማድረግ የመምህራን መብትንና ጥቅማ ጥቅማቸው ተከብሮ የመማር ማስተማር ሂደቱ የሚፈለገውን ግብ እንዲመታ እና ዩኒቨርሲቲው ማህበሩን በማገዝ በኩል ትልቅ ድርሻ እንደሚወጣ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የተፈጥሮ ሳይንስና ኮምፒውቴሽናል ኮሌጅ ዲንና የመምህራን ማህበሩ አስመራጭ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ዶ/ር ለገሰ ታደሰ በዚሁ ወቅት እናዳሉት አዲስ የሚዋቀረው የመምህራን ማህበር የመምህሩን መብትና ጥቅማ ጥቅም እንዲከበር ጥረት ከማድረግ ባለፈም የረጅም እድሜን ካስቆጠሩና ስኬታማ ከሆኑ መሰል ማህበራት ልምድን በመቅሰም ዩኒቨርሲቲው የሰነቀውን ርዕይ እንዲያሰካ የበኩሉን ኃላፊነት ሊወጣ ይገባል ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲን የመምህራን ማህበርን በአዲስ መልክ ለማዋቀር በተጠራው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ከኢትዮጵያ መምሀራን ማህበር አቶ ሽመልስ፣ ከድሬዳዋ መምህራን ማህበር አቶ አበበ ታምራት እና ከኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች መምህራን ማህበር ዶ/ር ፍቃዱ ዘለቀ የመምህራን ማሀበር የተመለከቱ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎችን ያቀረቡ ሲሆን በመጨረሻም የዩኒቨርሲቲውን የመምህራን ማህበር ለ 3 ዓመት የሚመሩት 7 አባላት ያቀፈ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ምርጫም ተካሂዷል፡፡ በዚህ መሠረትም መ/ር ድንቁ ዘውዴ ፕሬዝደንት፣ መ/ር ጸጋዬ አርጋው ም/ፕሬዝደንት፣ መ/ርት ፌቨን አብረሃም ዋና ጸሐፊ እና ስርዓተ ጾታ ተጠሪ፣ መ/ር አብረሃም ደምሰው የውጪና የህዝብ ግንኙነት፣ መ/ር መልካምሰው መሆን  የሂሳብ ሹም፣ መ/ር መላኩ አድነው  ኦዲተር እና መ/ር አሚኖ መሐመድ  ገንዘብ ያዥ ሆነው ተመርጠዋል፡፡

Share This News

Comment