Logo
News Photo

የስራ ዕድል ፈጠራን አስመልክቶ የውይየት መድረክ ተካሂዷል፡፡

የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ በድሬደዋ ስር የሰደዱና የነዋሪው ፈተና ሆነው የቆዩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ እያደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ ነው ሲሉ የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና የንግድ ፣ኢንደስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ ክቡር አቶ ሀርቢ ቡህ ተናገሩ፡፡ 

የድሬደዋ አስተዳደር የስራ ክህሎትና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ከድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና የንግድ ፣ኢንደስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀርቢ ቡህ እንዳስታወቁት በድሬደዋ ስር ሰደው የቆዩና ነዋሪውን በእጅጉ እየፈተኑ ያሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ከመፍታት አንፃር የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ እያደረገው ያለው ጥረት የሚደነቅና ለሌሎችም በአርያነት ሊወሰደት የሚገባ ተግባር ነው ባለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአስተዳደራችን ያሉትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ሳይንሳዊና በጥናት በተደገፈ መልኩ ለመፍታት በጉልህ የሚታይ ጥረት እያደረገ ነው ያሉት ክቡር አቶ ሀርቢ ቡህ በተለይም በአካባቢ ፅዳት፣ በግጭት አፈታት አሁን ደግሞ እንደ ሀገርም ሆነ እንደ አስተዳደር በእጅጉ እየፈተነን ያለውን የስራ-አጥነት ችግርን በዘላቂነት ለመቅረፍ እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው የጀመረውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም በበኩላቸው በድሬደዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሰቢነቱ እየጨመረ የመጣውን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ዩኒቨርሲቲው ከአስተዳደሩ የተለያዩ ሴክተር መስሪያቤቶች ጋር በመሆን እንቅስቃሴዎችን መጀመሩን ጠቁመው ቀደም ሲል የተደረጉ የጥናትና የምርምር ስራዎችን መነሻ በማድረግም በአሁ ሰዓት በአዲስ መልክ ወደስራ መገባቱን ተናግረዋል፡፡

በዚህ የውይይት መድረክ ላይም የሚቀርቡ ጥናቶች በተሳታፊዎች ሀሳብና በአስተያየት ዳብረው በድሬደዋ ያለውን የስራአጥ ቁጥር ትርጉም ባለው መልኩ መቀነስ እንዲቻል ጥረት ይደረጋል ያሉት ዶ/ር ኡባህ ቸግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍም ዩኒቨርሲቲው ከሚመለከታቸው ባለድረሻ አካለት ጋር በቅንጅት የጀመረውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

የድሬደዋ አስተዳደር የስራ ክህሎትና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሮቤል ጌታቸው በዚሁ ወቅት እንዳሉት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በጥናትና ምርምር ችግሮችን እየለዩ ፣ መፍትሔም እየሰጡ በስራ ዕድል ፈጠራ ላይ አማራጭ ሃሳቦችን እያቀረቡ እና ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር ትስስሮች እንዲጠናከሩ በማድረግ የአስተዳደራችን ነዋሪ ዋነኛ ፈተና የሆነው የስራ አጥነት ችግር በዘላቂነት እንዲፈታ የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል፡፡ በዚህ ረገድም የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥልበት ጠይቀዋል፡፡

ለአንድ ቀን በቆየው የውይይት መድረክ ላይ የስራዕድል ፈጠራ ላይ ትኩረት ያደረጉ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡   


Share This News

Comment