Logo
News Photo

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ለገንደ-ተስፋ የእግር ኳስ ቡድን ግምቱ 200 ሺህ ብር የሚጠጋ የስፖርት ትጥቅ ድጋፍ አደረገ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም ድጋፉን ለስፖርት ክለቡ ባስረከቡበት ወቅት እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፉ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልፀው በተለይም በዩኒቨርሲቲው አቅራቢያ የሚገኘውን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልፀው ከእነዚህም መካከል በስፖርት መድረክ ተሳትፎ እያደረጉ ለሚገኙ የገንደ ተስፋ የታዳጊና የወጣት የእግር ኳስ ቡድን እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠቃሽ ነው ብለዋል፡፡ 


የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሰለሞን ዘሪሁን በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደምም ለገንደ-ተስፋ የእግር ኳስ የስፖርት ክለብ የተለያዩ የስፖርት ትጥቅ ድጋፍ ማበርከቱን አስታውሰው  በዛሬው እለትም አጠቃላይ ወጪው 200 ሺህ ብር የሚሆን የስፖርት ትጥቅ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል ፡፡


ዶ/ር ሰለሞን ይህ ድጋፍ የአካባቢውን ወጣቶችና ታዳጊዎች ነገ የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ታስቦ የተደረግ መሆኑን ገልፀው ይህን መሰል ድጋፍም በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡ 


የገንደ ተስፋ አካባቢ ነዋሪዎች ዩኒቨርሲቲው የራሳቸው መሆኑን አውቀው በተቋሙ ላይ ጥፋትና ጉዳት ሲፈፀም በመከላከልና በመጠበቅ የበኩላቸውን ኃላፊነት ይወጡ ዘንድ መልእክታቸውን ያስተላለፉት በዩኒቨርሲቲው የቢዝነስና ልማት ም/ፕሬዝዳንት የሆኑት  ዶ/ር ተማም አወል ናቸው። 


በእለቱ ለገንደ-ተስፋ ለታዳጊና ለወጣት የእግር ኳስ ቡድን በድጋፍ መልክ የተበረከቱት የስፖርት ትጥቆች አጠቃላይ 200 መቶ ሺህ ብር ወጪ የተደረገባቸው የስፖርት ትጥቁ 50 ማሊያ 40፤ ኳሶች፣  እና 60 ትልቁን ትንሹ ኮኖች መሆናቸውን በዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ወንድይፍራው ደጀኔ ገልፀው የተደረገውን ድጋፍ በአግባቡ በመጠቀም ለውጤታማነት እንዲሰሩና የዩኒቨርሲቲውን ብሎም ድሬዳዋን እንዲያስጠሩ መልእክት አስተላልፈዋል። 


የገንደ-ተስፋ የእግር ኳስ ቡድን አሰልጣኝ የሆኑት አቶ ባህሩዲን አብዶ በበኩላቸው ክለባቸው ለድሬደዋ ከነማ ቡድን 8 ተጫዋቶችን እንዲሁም ከ17 ዓመት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደግሞ 2 ተጫዋቾችን ማፍራት የቻለ መሆኑን  ጠቅሰው ለዚህ ስኬቱ ደግሞ የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ድጋፍ ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ ተናግረዋል፡፡ 


በመጨረሻም የቡድኑ ታዳጊና ወጣት ተጫዋቾች ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ላደረጋቸው ድጋፍ አመስግነው ለወደፊት  ስመጥር እግር ኳስ ተጨዋች በመሆን የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲን ስም ለማስጠራት  እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡


Share This News

Comment