በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የቢዝንስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ያዘጋጀው 7ኛው ዙር ሀገራዊ ኮንፈረንስ ተካሄደ፡፡
በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ሳይንሳዊ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ጥናትና ምርምር ለዘላቂ ልማት በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀው 7ኛው ዙር ሀገራዊ ኮንፈረንስ ላይ በመገኘት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም እንደገለፁት በሀገራችን የድህነት ቅነሳን በማድረግ ዘላቂ ልማትና እድገትን ለማረጋገጥ የንግዱና የምጣኔ ሀብታዊውን ዘርፍ ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ማዘመን ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲም በተለይም የአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ እንደመሆኑ በንግድና በምጣኔ ሀብታዊ ዘርፍ በሳይንሳዊ መንገድ መደገፍ የሚችሉ የጥናትና የምርምር ስራዎችን በማከናወን የህዝቦችን ተጠቃሚነት እንዲያድግ የጀመረውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
ዶ/ር ኡባህ አክለውም የዚህ አይነት ሀገራዊ መድረኮች በዩኒቨርሲቲያችን ለሚገኙ ምሁራንና ተመራማሪዎች የሚኖራቸው ጥቅም ዘርፈ ብዙ መሆናቸውን ጠቅሰው በተለይም ልምድ የሚቀሰምበትና በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ከሚገኙ ምሁራን ጋር የእርስ በእርስ ትስስርን የሚፈጠረበት በመሆኑ የጎላ ፋይዳ ይኖራቸዋል ብለዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግልት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሰለሞን ዘሪሁን በበኩላቸው በየግዜው የምናደርጋቸው የምርምር ስራዎች ወደ መሬት ወርደው የማህበረሰቡን ችግር መፍታት የሚችል አቅም እንዲኖራቸው ትክክለኛ የማህበረሰቡን አሁናዊ ችግር ግምት ውስጥ ያስገባ መሆን እንዳለባቸው ገልፀው ከዚህ አንፀርም የምስራቁ አካባቢ የሀገራችን ዋነኛ የንግድ መናህሪያ እንደመሆኑ የንግዱና የምጣኔ ሃባታዊ ዘርፉን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ጥናትና ምርምር ተደርጎበት አዘመንን ከአካባቢያችን አልፈን ለሀገር ሊጠቅም በሚችልበት ምልኩ ልንቃኘው ይገባል ብለዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲውም በዚህ ረገድ በዘርፉ ላይ የጀመረውን ስራ አጠናክሮ በመቀጠል ትርጉም ያለው ለውጥና አድገት እንዲመዘገብ ጥረቱን ይቀጥላ ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን ረዳት ፕሮፌሰር ነፃነት ሽፈራ ሳይንሳዊ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ጥናትና ምርምር ለዘላቂ ልማት በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው ሀገራዊ ኮንፈረንስ በዩኒቨርሲቲው ደረጃ ለ7ኛ ጊዜ በኮሌጅ ደረጃ ደግሞ ለ2ኛ ጊዜ መካሄዱን ጠቁመዋል።
በዚህ ሀገራዊ ኮንፍረንስ ላይ በመገኘት ቁልፍ መልእክት ያስተላለፉት ታዋቂው የኢኮኖሚክስ ባለሞያ ዶ/ር ሰኢድ ኑሩ ጨምሮ በሀገራችን ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ ምሁራን እና ተመራማሪዎች የምርምር ስራቸውን አቅርበዋል፡፡
Share This News