Logo
News Photo

በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ በተፈጥሮና ኮምፒውቴሽናል ሳይንስ ኮሌጅ ውስጥ ለሚሰሩ መምህራን እና ረዳት የቤተ-ሙከራ ባለሙያዎች የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ተሰጠ፡፡

የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝዳንት በመወከል ዶ/ር አለማየሁ ዘውዴ መድረኩን በንግግር ሲከፍቱ እንዳሉት በዩኒቨርሲቲያችን የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ከመማር-ማስተማር ጋር በተያያዘ ወቅቱን ያገናዘበና ተከታታይነት ያላቸው የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎች ለመምህራን እና ለረዳት የቤተ-ሙከራ ባለሙያዎች መሰጠት አስፈላጊ ነዉ ብለዋል፡፡ 

ዶ/ር አለማየሁ አክለውም የተፈጥሮና ኮምፒውቴሽናል ሳይንስ ኮሌጅ ከአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ስልጠና በዩኒቨርሲቲው በመማር- ማስተማሩ ዘርፍ ቀጣይነት ያለው ስኬታማ ተግባራትን ለመከወን ትልቅ ፋይዳ ስለሚኖረዉ መሰል ስልጠናዎች  ተጠናክረው ሊቀትሉ ይገባል ብለዋል፡፡

የተፈጥሮና ኮምፒውቴሽናል ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ለገሰ ታደሰ እንደገለጹት ይህ ስልጠና የተዘጋጀበት ዋና ዓላማዉ በመማር-ማስተማሩ ሂደት የተሰተዋሉ ክፍተቶችን በመቀነስ በሚቀጥለዉ ዓመት ሊሰጥ የታሰበዉን የከፍተኛ ትምህርት  ተቋማት ተመራቂ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና በተሻለ መልኩ ተማሪዎችን ለማዘጋጀት የሚደረገዉን ተቋማዊ ኃላፊነት ለመወጣት አንደሚያግዝ እና በስልጠናው ተቋሙ ባፈራቸው  መምህራን ሙሉ ለሙሉ መሰጠት መቻሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ የተቋሙ አቅም ምንያህል እድገት እዳመጣ በግልጽ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡ 

ከዚህ በተጨማሪም ስልጠናው መምህራን እና ረዳት የቤተ-ሙከራ ባለሙያዎች በስራቸው ላይ የሚያገጥሟቸውን ችግሮች ከመቅረፍና የማስተማር አቅማቸውን ከማሳደገፍ አንጻር ያለው ፋይዳ የጎላ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ለገሰ በተለይም ስልጠናው ከንድፈ ሀሳብ ባለፈ በተግባር የተደገፈ በመሆኑ በዩኒቨርሲቲው የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እየተደረገ ላለው ጥረት ትልቅ እገዛ እንደሚኖረውም ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም ስልጠናውን ሲሰጡ ለነበሩ አስልጣኝ መምህራን፣ በስልጠናዉ ላይ በንቃት የተሳተፉትን ሰልጣኞች የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ለገሰ ታደሰ ምስጋናቸውን ያቀረቡ ሲሆን በቀጣይም  ከሚመለከታቸው የዩኒቨርሲቲዉ የስራ ክፍሎች ጋር በመተባበር ነባራዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያደረጉ  መሰል ስልጠናዎችን ለማሰጠት አቅም በፈቀደ መልኩ ኮሌጁ ጥረት ያደርጋል ብለዋል፡፡

በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ በተፈጥሮና ኮምፒቴሽውናል ሳይንስ ኮሌጅ አማካኝነት ለሦስት ቀናት ሲሰጥ በቆየው የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ላይ 71 የኮሌጁ መምህራንና ረዳት የቤተ-ሙከራ ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል፡፡


Share This News

Comment