Logo
News Photo

በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ሀገር በቀል እውቀቶችን ለልማት ማዋል ላይ ትኩረት ያደረገ ፎረም ተካሄደ፡፡

በፎረሙ መክፈቻ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት በዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝዳንትና የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ተወካይ ዶ/ር መገርሳ ቃሲም በሀገራችን ቀጣይነት ያለው ልማትና እድገትን ለማረጋገጥ ሀገር በቀል አውቀቶችን መሠረት ያደረጉ ስራዎች በስፋትና በጥራት  መሰራት አለባቸው ብለዋል፡፡

በምስራቁ አካባቢ የሚገኙትን ሀገር በቀል እውቀቶች ዘመናዊ በሆነ መልኩ በማልማት ማህበረሰቡን እንዲጠቅሙ ለማስቻል ዩኒቨርሲቲው በጥናት የተደገፉ ጅምር የምርምር ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ የጠቆሙት ዶ/ር መገርሳ እነዚ ሀገር በቀል እውቀቶች ለተተኪው ትውልድ እንዲተላለፉ በስረዐተ ትምህርት ውስጥ እንዲካተቱ ሰፊ እንቅስቃሴ ይደረጋል ብለዋል፡፡

 ለፎረሙ ተሳታፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሰለሞን ዘሪሁን በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ሀገር በቀል እውቀቶች ላይ ሙሉ ትኩረቱን ያደረገ ቡድን በማቋቋም በዳይሬክቶሬት ደረጃ  እንዲመራ በማድረግ ሀገር በቀል እውቀቶቹን ለማህበረሰቡ መጥቀም እንዲችል እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ገልፀው በተለይም በአካባቢው ያሉ በግጭት አፈታትና በባህላዊ የመድሐኒት ቅመማ ላይ ትኩረት ያደረጉ ስራዎች በቀጣይ ለመስራት ታቅዷል ብለዋል፡፡

 ከዚህ በተጨማሪም የምስራቅ ኢትዮጵያ  አካባቢን ብሔር ፣ብሔረሰብ እና ህዝቦችን በደንብ ማሳየት የሚችል ሙዚየም ለመገንባት ዩኒቨርሲቲው ማቀዱን የተናገሩት ዶ/ር ሰለሞን ይህ እቅድ እውን እንዲሆን ሁሉም ወገን የድርሻውን ይወጣ ዘንድ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

ለአንድ ቀን በቆየው ፎረም ላይ የሀገር በቀል እውቀቶችን የተመለከቱ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

Share This News

Comment