Logo
News Photo

የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ መምህር በሆነው በብርሃኑ ፋንቴየተፃፈው "የአመራር ምህንድስና" የተሰኘው መጽሐፍ ተመረቀ፡፡

መምህር ብርሃኑ ፋንቴ በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ከ10 ዓመት በላይ በማስተማርና በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ በማገልግል ላይ የሚገኝ ሲሆን አሁን ደግሞ "የአመራር ምህንድስና" በሚል የአመሪነት ጥበብ ላይ ትኩረት ያደረገ መፅሐፍ በማሳተም ለአንባቢያን አቅርቧል፡፡

መምህር ብርሃኑ ፋንቴ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ መጽሐፉን ለማሳተም እገዛ ላደረገለት ለድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ፣የመጽሐፋን ረቂቅ ጽሁፍ አርትኦት በማድረግ የተለያዩ አስተያየቶችና ሀሳቦችን ለሰጡት የስራ ባልደረቦቹ እና የተለያዩ ባለሙያዎች፣ እንዲሁም መጽሐፋ ለህትመት እስኪበቃ ድረስ በገንዘብ እና በሞራል ድጋፍ በማድረግ ከጎኑ ላልተለዩት ቤተሰቦቹ እና ጓደኞቹ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም መምህራን ከተለመደው የመማር እና ማስተማር ስራ ጎንለጎን ሀገራቸውን እና ማህበረሰባቸውን የሚለውጥ ስራ መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡ 

መምህር ብርሃኑ ፋንቴ ለብዙዎቻችን አርዕያ የሚሆን ስራን ነው ያበረከተው ያሉት ዶ/ር ኡባህ ለዚህ ተግባሩም የእንኳን ደስ ያለህ መልእክት አስተላልፈዋል፤ ሌሎች መምህራን መሰል ስራዎች ላይ በርትተው እንዲሰሩ አስገንዝበው፣ ዩኒቨርሲቲው መሰል ስራዎችን በቅርበት እየተከታተለ አቅሙ በፈቀደ ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡ 

በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር መገርሳ ቃሲም መምህራን ትውልድን በእወቀትና በስነ-ምግባር ከማነፅ ተቀዳሚ ተግባራቸው ጎን ለጎን ለምኅበረሰብ ለውጥና እድገት የሚጠቅሙ የፈጠራ ስራዎችን በማበርከት የበኩላቸውን መወጠት ይኖርባቸዋል፡፡

መምህር ብርሃኑ ፋንቴ ብዙ ጥረትና ድካም የሚጠይቀውን መጽሐፍ የመጻፍ ስራ እውቀቱን እና ልምዱን በመጠቀም ለብዙዎች አርዕያ የሚሆን ስራን ነው ያበረከተው ያሉት ዶ/ር መገርሳ ሌሎች መምህራንም የእርሱን ፈለግ በመከተል ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን ለማህበረሰባችን የሚጠቅሙ ስራዎችን ያበረክቱ ዘንድ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር ሰለሞን ዘሪሁን በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው ደረጃ ለዩኒቨርሲቲው የማኔጅመንት ኮሚቴ ቀርበው ለህትመት እንዲበቁ ውሳኔ ከተሰጠባቸው ሁለት መጽሐፎች ውስጥ ዛሬ ለምረቃ የበቃው የመምህር ብርሃኑ ፋንቴ "የአመራር ምህንድስና "የተሰኘው መጽሐፍ አንዱ ሲሆን መጽሐፉ የሀገር እድገት የመሪውን ብቃት፣ ጥበበኝነት እና አርቆ አስተዋይነትን የሚጠይቅ መሆኑን ግልፅ አድርጎ የሚያሳይ በመሆኑ ለማህበረሰባችን ለውጥና እድገት የራሱን አሻራ ማኖር የሚችል ትልቅ ስራ ነው ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲውም ከሀገርና ከህዝብ ከተሰጠው ተልዕኮ መካከል በጥናትና ምርምር ስራዎች የማህበረሰቡን ችግር በዘላቂነት መፍታት እንዱ ተልዕኮው ነው ያሉት ዶ/ር ሰለሞን ለማህበረሰቡ ትልቅ ፋይዳ ያላቸውን መሰል ሰራዎች የመደገፉ ተግባራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን በማለት አረጋግጠዋል፡፡

በመጽሐፍ ምረቃስነ-ስረዓቱ ላይ ታዋቂው የስራአመራርና ቢዝነስ ጉዳዮች አሰልጣኝ፣ ጸሐፊ እና አማካሪ የሆኑት ዶ/ር ወሮታው በዛብህ፤ የድሬደዋ አስተዳደር ስራ አመራርና ካይዘን ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር አቶ አወቀ ለገሰ፣ በዩኒቨርሲቲው የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር አለማየሁ ዘውዴ፣ እንዲሁም በእለቱ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የታደሙ ተሳታፊዎች መጽሐፉን በተመለከተ ሀሳብና አስተያየታቸውን ሰጥተውበታል፡፡


Share This News

Comment