Logo
News Photo

የዋሻ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ እንዲሁም የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ሙዝየም ማቋቋምን ዓላማ ያደረገ ስልጠና ተሰጠ።

ለስልጠናው ታዳሚዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት በዩኒቨርሲቲው የምርምር ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ረ/ፕሮፌሰር ይታገሱ ስንታየሁ ሲሆኑ በንግግራቸውም በድሬዳዋ አስተዳደር ውሰጥ የሚገኙ ዋሻዎች እድሜያቸው ከ5000-8000 ዓመታት ያሰቆጠሩ እንደሆኑ ጠቅሰው፣ በተፈጥሮ እና በሰው ሰራሽ ምክንያቶች  ዋሻዎቹ በይዘታቸው እየደበዘዙ አለፍ ሲልም እየፈረሱ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

እንደ ረ/ፕሮፌሰር ይታገሱ ገለፃ የዚህ ስልጠና ዋና አላማም ከቅርስ ጥናትና ጥበቃ ጋር በተያያዘ የሚመለከታቸው መምህራንን እና ባለሞያዎችን ስልጠና በመስጠት ቅርሶችን እንዲጠብቁና እንዲንከባከቡ መሆኑን ገልፀው ከስልጠናው በኋላም ዩኒቨርሲቲያችን ተቋማዊ ተልዕኮውን ለመወጣት ያስችለው ዘንድ የምርምር፣ የቅርስ ጥበቃና ጥገና መስራት የሚያስችል ሃሳቦች እንደሚገኝበት በመተማመን መሆኑን ጭምር በመልዕክታቸው አስተላልፈዋል፡፡

በመቀጠል በዩኒቨርሲቲው የሀገር በቀል ዕውቀት ማዕከል አስተባባሪ የሆኑት ረ/ፕሮፌሰር ንጉስ ገ/መድህን ስልጠናው በዋናነት በድሬዳዋ አስተዳደር የሚገኙ የሚዳሰሱ ቅርሶችን እንዴት መጠበቅና መንከባከብ  እንደሚቻል ላይ ያተኮረ  መሆኑን ገልፀው፣ ከስልጠናው መጠናቀቅ በኋላ ተመራማሪዎች የምርምር ንድፈ ሃሳብ እንዲያዘጋጁ እንዲሁም ሰልጣኞች ዩኒቨርሲቲያችን መስራት የሚጠበቅበትን የስራ ድርሻ ማመላከት እንደሚኖርባቸው በመልዕክታቸው ላይ አስተላልፈዋል፡፡   

ስልጠናው ከኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን መ/ቤት በመጡ ዶ/ር ታደለ ሰለሞን (አርኪዮሎጂስት) እና በአቶ ንጉሱ መኮንን (ሙዝዮሎጂስት) የተሰጠ ሲሆን፣ በስልጠናው ላይ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ ከድሬዳዋ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እንዲሁም ከድሬዳዋ ቅርስ ባለአደራ ማህበር የተውጣጡ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

በዚህ ለሁለት ቀን በቆየው ስልጠና መጠናቀቂያ ላይ ሰልጣኞች ወደ ሀርላ ታሪካዊ ቦታ የመስክ ጉበኝት አድርገዋል፡፡

Share This News

Comment