Logo
News Photo

የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ በSTEM ማዕከል ላለፉት ሶስት ወራት በኤሌክትሮኒክስና መረጃ ቴክኖሎጂ ስልጠና ሲከታተሉ የነበሩ የ1ኛና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን አስመረቀ።

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ STEM ማዕከል በድሬዳዋ አስተዳደር ስር ከሚገኙ የ1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በሳይንስ (ፊዚክስ፤ ባዮሎጂና፤ ኬሚስትሪ) እና በሒሳብ ትምህርት ዓይነቶች ባላቸው የተሻለ ውጤት ተመልምለው ላለፉት ሶስት ወራት በኤሌክትሮኒክስና መረጃ ቴክኖሎጂ በተግባር የተደገፈ ስልጠና ሲከታሉ የነበሩ ቁጥራቸው  82 የሚደርስ ተማሪዎችን በዛሬው ዕለት አስመርቋል፡፡

በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ወንዲፍራው ደጀኔ ሲሆኑ በንግግራቸውም የድሬ ዳዋ ዩኒቨርሲቲ የሳ.ቴ.ም.ሂ (STEM) ማዕከል በሳይንስና በሒሳብ ትምህርት አይነቶች የተሻለ ውጤት ያላቸውን የ1ኛ እና የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በንድፈ-ሀሳብ የቀሰሙትን  እውቀት  በተግባር ልምምድ የሚያዳብሩበት ሁኔታ በማመቻቸት ለሶስት ወራት በቅዳሜና እሁድ ፕሮግራም ስልጠናውን ሲሰጥ መቆየቱን ገልፀው ለምረቃ የበቁትን ተማሪዎች እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡ 

በምርቃት ስነ-ሥርዓቱ ላይ የSTEMPower Ethiopia ተወካይ አቶ አንተነህ ፍስሃ ተገኝተው ንግግር ያደረጉ ሲሆን ስልጠናውን ያጠናቀቁትን ተማሪዎች እንኳን ደስ አላችሁ ካሉ በኋላ STEMPower Ethiopia ለድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ STEM ማዕከል መጠናከር ከዚህ በፊት ያደርግ የነበረውን ድጋፍ ወደፊትም በስፋት እንደሚቀጥል ገልፀው ተማሪዎች የተሰጣቸውን እድል በአግባቡ በመጠቀም የሳይንስ እውቀታቸውንና የፈጠራ ክህሎታቸውን በማሳደግ ነገ ሃገራችንን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲያደርሷት አደራ ብለዋል፡፡

የዩነቨርሲቲው STEM ማዕከል አስተባበሪ መ/ር ግዛው ገ/ስላሴ በበኩላቸው ተማሪዎቹ በስልጠናው ጥሩ እውቀትና ክህሎት የቀሰሙ መሆናቸውን ተናግረው ስልጠናውን ካጠናቀቁት ተማሪዎች መካከል የፈጠራ ፕሮጀክት ሃሳብ ያላቸው ተማሪዎች በመምህራኖቻቸው አማካኝነት የተመረጡ መሆኑን ገልፀው በቅርቡ ወደ ፕሮጀክት ሥራቸው እንደሚገቡ ገልፀዋል፡፡ 

አስተባባሪው አያይዘው እንደተናገሩት ማዕከሉ የቀጣይ ዙር  የሳ.ቴ.ም.ሂ (STEM) ሰልጣኞችን ለመቀበል ዝግጅት ያጠናቀቀ መሆኑን ገልፀው ትምህርት ቤቶች ሰልጣኝ ተማሪዎቻቸውን በተቀመጠው መስፈርት መሰረት መልምለው ለዩኒቨርሲቲው እንዲልኩልን መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በመጨረሻም ስልጠናውን በአግባቡ ያጠናቀቁ ተማሪዎች የተዘጋጀላቸውን ሰርተፍኬት ከእለቱ የክብር እንግዳ የSTEMpower Ethiopia ተወካይ አቶ አንተነህ ፍስሃ ተቀብለው ፕሮግራሙ ተጠናቋል፡፡


Share This News

Comment