በድሬዳዋ አስተዳደር ካለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ '' በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ'' በሚል መሪ ቃል የ2015 የክርምት በጎ ፈቃድ አገልግልት ሲካሄድ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
በዚሁ የክረምት በጎ ፋቃድ አገልግሎት መርሀግብር ውስጥ የራሱን ድርሻ በመውሰድ የ4 አቅመ ደካማ ነዋሪዎች መኖሪያ ቤት የመገንባትና የማደስ ሥራ ሲያከነውን ቆይቶ በዛሬው እለትም የአስተዳደሩ ም/ከንቲባና የንግድ፣ ኢንደስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ የተከበሩ አቶ ሀርቢ ቡህ እና በየደረጃው የሚገኙ የአስተዳደሩ አመራሮች በተገኙበት አስመርቋል፡፡
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ም/ከንቲባና የንግድ፣ ኢንደስትሪና ኢንቨስትምንት ቢሮ ኃላፊ የተከበሩ አቶ ሀርቢ ቡህ እንዳሉት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በመማር ማስተማር ፣ በጥናትና ምርምር ለአገርና ለአስተዳደሩ እያበረከተ ካለው አስተዋፅዖ ጎን ለጎን በማኅበረሰብ አገልግልትም የበርካታ አቅመደካማ ነዋሪዎችን ችግር መቅረፍ የቻሉ የተለያዩ ተግባራትን አከናውኗል፤ እያከናወነም ይገኛል ብለዋል፡፡
የተከበሩ አቶ ሀርቢ ቡህ አክለውም ዩኒቨርሲቲው እነዚህን የአቅመ ደካማ ወገኖች ችግር የመቅረፍ ተግባሩን በቀጣይ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም በ2015 ዓመት የክረምት በጎፈቃድ አገልግልት ዩኒቨርሲቲው ከ1.2 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የ5 የአቅመ ደካማ ነዋሪዎችን ቤት ደረጃውን በጠበቀ መንገድ ግንባታና አድሳት አከናውኖ በማጠናቀቅ ለነዋሪዎቹ አስረክቧል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ለመኝታ አገልግሎት የሚውል የስፖንጅ ፍራሾችንም በድጋፍ መልክ ማበርከቱን በዚሁ ወቅት ዶ/ር ኡባህ ተናግረዋል፡፡
ድጋፉ የተደረገላቸው አቅመ ደካማ ነዋሪዎች በበኩላቸው ከዚህ ቀደም የሚኖሩበት ቤት እጅግ ሲበዛ በማርጀቱና የሚያፈስ በመሆኑ በተለይ በክርምት ወቅት ይደርስባቸው የነበረው ፈተና ከባድ የነበረ መሆኑን ተናግረው በአሁኑ ሰዓት ግን የወረዳ 02 መስተዳድር ያለባቸውን ችግር ከግምት ውስጥ በማስገባት የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ደረጃውን የጠበቀ ቤት ባለቤት እንዲሆኑ በማድረጉ ምሳጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
Share This News