በደንበኞች አገልግሎት ልህቀት እና የሙያ ስነ-ምግባር ዙሪያ ለዩኒቨርሲቲዉ የአስተዳደር ሰራተኞች ስልጠና ተሰጠ::
በስራ ቅጥር እና ፈጠራ ልማት ማዕከል ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት በደንበኞች አገልግሎት ልቀት እና በሙያ ስነ-ምግባር ላይ ያተኮረ ስልጠና ከዩኒቨርሲቲው ስራ-አስፈፃሚ ቢሮዎች ለተወጣጡ የአስተዳደር ሰራተኞች ተሰጥቷል፡፡
ስልጠናው በደንበኞች አገልግሎት እና ሙያዊ ስነ-ምግባር ዙሪያ የአስተዳደር ሰራተኞችን አቅምን ለማሻሻል፤ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ቀልጣፋ፣ ስነ-ምግባርን የተላበሰ እንዲሁም ደንበኛን ማእከል ያደረገ አገልግሎቶችን ማቅረብ ማስቻል ላይ ያተኮረ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ስልጠናው ከዚህ በተጨማሪ የሰራተኛ እና ደንበኛ ግንኙነትን፣ የጊዜ አጠቃቀምን፤ የስነምግባር ባህሪን፣ የቡድን ስራን እንዲሁም ተጠያቂነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ነው፡፡
ስልጠናውን በይፋ የከፈቱት የዩኒቨርሲቲዉ አስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሰለሞን ዘሪሁን እንደተናገሩት ‘’ተቋማዊ ውጤታማነትን እና የባለድርሻ አካላትን እርካታ ለማጠናከር የአገልግሎት ልህቀት እና የሙያ-ስነምግባር አስፈላጊ ነው’’ ብለዋል። ዶ/ር ሰለሞን አክለውም ‘’ስልጠናው በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ሙያዊ ምግባር እና ጥራት ያለው አገልግሎት አሰጣጥ እንዲጎለብት ከፍተኛ ድርሻ አለው ያሉ ሲሆን ስልጠናዉን ላዘጋጁ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲዉ የስራ ቅጥርና ልማት ማዕከል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ቃልኪዳን መዝገቡ የማዕከሉን አላማዎች እና አገልግሎቶች በመዘርዘር ለተሳታፊዎች ንግግር አድርገዋል። ሰልጣኞች በስልጠናዉ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉና በግል ህይወታቸዉ እንዲሁም ለተቋሙ ለዉጥ የሚረዱ ሃሳቦችን ከስልጠናዉ እንዲወስዱና ዩኒቨርሲቲዉን በመቀየር ሂደት ዉስጥ መሪ-ተዋናይ እንዲሆኑ አሳስበዋል፡፡
Share This News