ከዩኒቨርሲቲ አካባቢ ማኅበረሰብ ጋር በሰላማዊ መማር ማስተማር ዙሪያ ውይይት ተደረገ
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በዩኒቨርሲቲው ዙሪያ ከሚገኙ የማህበረሰብ ክፍል ተወካዮች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡ ውይይቱ የተደረገው በዩኒቨርሲቲው አካባቢ ከሚገኙት የመርማርሳ ፣ ገንደ ተስፋ እና ቶኒ መንድር ተወካዮች ጋር ሲሆን ውይይቱም ሰላማዊ የመማር ማስተማርና የማኅበረሰብ አገልግልት ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር ፡፡
በውይይቱ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ተወካይና የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር መገርሳ ቃሲም እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ከህዝብና ከመንግስት የተሰጡትን ሦስት ተልዕኮዎች ለማሳካት የግድ የማኅበረሰቡ ድጋፍና እገዛ ያስፈልገዋል ያሉ ሲሆን ለዚህም ደግሞ በተለይ በዩኒቨርሲቲው አካባቢ የሚገኘው ማኅበረሰብ እንደ ቀደመው ጊዜ ሁሉ ከዩኒቨርሲቲው ጎን በመሆን እያደረገ ያለውን አስተዋፅኦ ከበፊቱ በበለጠ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
በውይይቱ ላይ ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ሁለት ዓመታት ለአካባቢው ማህበረሰብ ያከናወናቸው ዋና ዋና ተግባራት እንዲሁም በቀጣይ በዕቅድ የተያዙ ለአካባቢው ማህበረሰብ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳ ያላቸው ሥራዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የመንደሮቹን ነዋሪዎች በመወከል በውይይት መድረኩ ላይ የተሳተፉት የተለያዩ አስተያየትና ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡
የማኅበረሰቡ ተወካዮች በሰጡት አስተያየት ዩኒቨርሲቲው በብዙ መልኩ እያደረገላቸው ያለው ድጋፍና እገዛ ትልቅ ቦታ የሚሰጡት እና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን ገልፀው ዩኒቨርሲቲው ከንፁህ መጠጥ ውኃ ፣ ከሥራ ዕድል ፈጠራ ፣ ከመንገድ መብራት ዝርጋታና፤ ጎርፍና መሰል ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ጋር ተያይዞ ያሉባቸውን ችግሮች እንዲቀርፍላቸውና ከቀድሞ በበለጠ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ ጠይቀዋል፡፡
ከማኅበረሰብ ተወካዮቹ ለተነሱት ጥያቄዎች በዩኒቨርሲቲው የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተማም አወል ምላሽ የሰጡ ሲሆን ዶ/ር ተማም በምላሻቸው ዩኒቨርሲቲው በበጀት አቅም ሊፈቱ የሚችሉና አንገብጋቢ ናቸው ያሏቸውን ችግሮች በማስቀደም እንዲሁም ከአጋር አካላት ጋር ሊፈቱ የሚችሉትን ችግሮች በመለየት ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ጥረት ያደርጋል ብለዋል፡፡ ዶ/ር ተማም አያይዘውም የአካባቢው ማኅበረሰብ በበኩሉ ዩኒቨርሲቲውን በሙሉ ባለቤትነት መንፍስ በመቀበል ዘላቂና አስተማማኝ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት አጋዥነቱን አጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
ለግማሽ ቀን በቆየው የውይይት መድረክ ላይ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ አካባቢ ከሚገኙት የተለያዩ መንደሮች የተውጣጡ የማኅበረሰቡ ተወካዮችና የወረዳ 02 አመራሮች ተሳታፊ ሆነውበታል፡፡
Share This News