በዩኒቨርሲቲው የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተዘጋጀው መድረክ ላይ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተመራቂ ተማሪዎች በቡድን የተግባር ልምምድ ወደ ማኅበረሰብ በመውረድ በማህበረሰብ እና ጤና ተቋማት ውስጥ የሰሩት ሥራ በዝርዘር አቅርበዋል፡፡
ይህ የቡድን የተግባር ልምምድ 150 ተማሪዎች ከተለያየ ትምህርት ክፍል ማለትም ከነርስ ፣ከሚድዋይፈሪ፣ ከሳይካትሪ ነርስ፣ ከላብራቶሪ ትምህርት ክፍሎች እንዲሁም ከህክምና ት/ት ቤት በጋራ በመሆን የተሳተፉበት ነው፡፡
ሳቢያን፣ ገንደ ቆሮ፣ ጎሮ እና አዲስ ከተማ ተብለው በሚጠሩት ሰፈሮች ህብረተሰቡ ከጤና ጋር ተያይዞ ተደጋግሞ የሚያጋጥመውን ችግር በመለየት መሠረታዊና አሳሳቢ ናቸው የተባሉትን ችግሮች ለመቅረፍ የተለያዩ ተግባራትን ፈፅመዋል፡፡
በዚህ መሠረትም በአራት አካባቢዊች አራት አዲስ የመፀዳጃ ቤት ጉድጓድ ቁፋሮ በማካናወን ሙሉ ግንባታን አጠናቀው ለህብረተሰቡ አስረክበዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም 20 የቆሻሻ ፍሳሽ ማስወገጃ ጉድጓድ ፣ በደም ልገሳ ፕሮግራም 250 ዩኒት ደም በማሰባሰብ ፣ በከተማዋ ቆሻሻ ተከማችቶባቸው የነበሩ አካባቢዎችን ከአስተዳደሩ ጽዳትና ውበት ኤጀንሲ ጋር በመሆን በማፅዳት እና ህብረተሰቡ አስቀድሞ በሽታን መከላከል እንዲችል ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራም ሠርተዋል፡፡
በዚሁ መድረክ ላይ የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር መገርሳ ቃሲም ባስተላለፋት መልዕክት ተመራቂ ተማሪዎቹ ወደ ማኅበረሰቡ ወርደው የሠሩት ሥራ የሚበረታታና ምስጋና የሚያስቸራቸው ነው፡፡ ተመራቂ ተማሪዎቹ የሠሩት ሥራ ከማኅብረተሰቡ በቅርብት እንዲተዋወቁ ያደረጋቸውና ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ሥራ ሲሰማሩ ችግሩን ለይተው ለመቅረፍ ጥረት እንዲያደርጉ ያግዛቸዋል ብለዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን የሆኑት ዶ/ር ሁሴን መሐመድ በበኩላቸው የተሠራው ሥራ ተመራቂ ተማሪዎቹ በንድፈሃሳብ የተማሩትን ወደ ተግባር እንዴት መቀየር እንደሚችሉ ዕድል የፈተረላቸውና በቡድን መሥራት በቀላሉ ለስኬት እንደሚያበቃ ልምድ የቀሰሙበት ነው ብለዋል፡፡
Share This News