አንጋፋው የፓለቲካል ሳይንስ ምሁር፣ አንባሳደር እና ዲፕሎማት ፕሮፌሰር ብሩክ ሀይሉ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በመገኘት ገለፃ አደረጉ
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በሀገር ደረጃ ከፍተኛ እውቅና እና አበርክቶ ያላቸውን ምሁራን በመጋበዝ ገለፃ እንዲያደርጉ እንዲሁም ልምድ እና እውቀታቸውን ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ እንዲያጋሩ መድረኮችን ያመቻቻል፡፡ በዚሁ መሰረት በፓለቲካል ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ ትልቅ ስም እና ዝናን ያተረፉት ፕሮፌሰር ብሩክ ሀይሉ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በመገኘት በተለያዩ ወቅታዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ገለፃ አድርገዋል፡፡
ፕሮፌሰር ብሩክ ከልጅነት አስተዳደግ ጀምሮ በትምህርት ጉዞዋቸው ከመጀመሪያ ደረጃ ት/ርት እስከ ከፍተኛ ትምህርት ዝግጅታቸው፣ የህይወት ተሞክሮ እና ፍልስፍናዎቻቸው አስተማሪ ገለፃ ያደረጉ ሲሆን ተማሪዎች በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ፣ በህይወታቸው ደስተኛ እና ስኬታማ ለመሆን ሊከተሏቸው ስለሚገቡ መርሆዎች በምሳሌ እያዋዙ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ሀገርን ማገልገል መቻል ታላቅ መንፈሳዊ እርካታን የሚሰጥ ተግባር ነው ያሉት ፕሮፌሰር ብሩክ ሀገርን በማገልገል የሚገኘው ውስጣዊ እርካታ ከ ብር፣ ሀብት እና ቁሳቁስ በላይ ፍፁም ደስታ ያለው መሆኑን በመጥቀስ ተማሪዎች በተለይ ዩኒቨርሲቲ ምሩቃን አቅማቸው በፈቀደ ልክ እና ባለቸው እውቀት እና ክህሎት ሀገራቸውን በማገልገል ሳይማር ያስተማራቸውን ሰፊውን ህዝብ ሊክሱ ይገባል ብለዋል፡፡
በወቅታዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ማብራሪያ የሰጡት ፕሮፌሰር ብሩክ ኢትዮጲያ የአፍሪካ የነፃነት ቀንዲል፣ አህጉራዊ አንድነት ፋና ወጊ እና መሪ በመሆን ያበረከተችውን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ታሪክ ሲዘክረው ይኖራል ያሉ ሲሆን አሁንም ቢሆን በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ የመሪነት ሚናን በመጫወት ጉልህ ድርሻ ያላት መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ኢትዮጲያ የወደብ ባለቤት እንዳትሆን ታሪክ ይቅር የማይለው ስህተት ተሰርቷል ያሉት ፕሮፌሰር ብሩክ ሀይሉ በማከልም ‘’በዋዛ ፈዛዛ የሚቀር የሀገር ሃብት አይኖርም መንግስት ከዚህ በፊት የተሰሩ ስህተቶችን ለማረም እያደረገ ያለው ጥረት ድጋፍ ሊቸረው ይገባል’’ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ፕሮፌሰር ብሩክ ሃይሉ ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮችም ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን ከዩኒቨርሲቲው ጋር በቀጣይነት ለመስራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡
Share This News